መጋቢት 7/2013 (ዋልታ) – ህንድ በኢትዮጵያ የምታካሂደው ኢንቨስትመንት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ትዝታ ሙሉጌታ ገለጹ።
አምባሳደሯ በሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ዲዲ ኢንዲያ ላይቭ ከተባለ የመገናኛ አውታር ጋር ባደረጉት ቆይታ ህንድና ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በባህል ዘርፍ የረዥም ጊዜ የግንኙነት ታሪክ እንዳላቸው አስታውሰዋል።
ግንኙነቱ እ.አ.አ በ1948 የጀመረ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሯ፣ ሁለቱ ሀገራት በርካታ የሚጋሯቸው ነገሮች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።
“የሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በተለይ ንግድና ኢንቨስትመንት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል” ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከውጭ ለሚገቡ ኢንቨስትመንቶች የምታደርጋቸው ማበረታቻወች በምክንያትነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አንስተዋል።
“ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው አለም አቀፍ ህጎች ኢንቨስተሮች ያለ ስጋት ወደ አገር እንዲገቡና ኢንቨስት እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል” ብለዋል።
ይህም ህንድ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ካላቸው አገሮች መካከል አንዷ እንድትሆን እንዳስቻላት ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ከ600 በላይ የህንድ ኩባንያዎች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን 75 ሺህ ለሚሆኑ ወገኖች የስራ እድል እንደፈጠረ ከኢዜአ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
አብዛኛዎቹ ፋብሪካዎች በማኒፋክቸሪንግ እና በግብርና መስኮች የተሰማሩ ናቸው።