በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ግብርና ላይ ብቻ ትኩረቱን ያደረገ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሊቋቋም ነው

መጋቢት 30/2014 (ዋልታ) ፐርፐዝ ብላክ ኢቲ.ኤች በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ግብርና ላይ ብቻ ትኩረቱን ያደረገ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሊያቋቁም መሆኑን አስታወቀ፡፡

ግብርና ላይ ብቻ ትኩረቱን ያደረገው የቴሌቪዥን ጣቢያ በዋናነት ግብርና ቁልፍ የልማት መሳሪያ ስለመሆኑ ይበልጥ ግንዛቤ ለመስጠት ያግዛል ተብሏል፡፡

ፐርፐዝ ብላክ ኢቲ.ኤች የመጀመሪያውን ዓመታዊ አግሪ ኢኖቬሽን ኮንፈረንስ ያካሄደ ሲሆን በኮንፈረንሱ የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የፐርፐዝ ብላክ ኢቲ.ኤች ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሰኃ እሸቱ (ዶ/ር) ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ግብርና ላይ መሰረት ያደረገው የኢትዽያ ሕዝብ መሰረታዊ ምጣኔ ሃብታዊ ለውጥ ማምጣት ካስፈለገ ከ40 በመቶ በላይ የሚባክንን ምርት መታደግና ግብርናን በቴክኖሎጂ ማገዝ አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

እንደ ሀገር ከዘመናት በላይ የተሻገሩ የግብርና ሀገር በቀል ዕውቀቶች ፈጠራን በማከል ግብርና ላይ ውጤታማ በሆነ መንገድ ምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ ለማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረቱን ያደረገው ኮንፈረንሱ በዘርፉ እውቀት ያላቸው ሙያተኞችንና ዘላቂ የሆነ የመፍትሄ ሀሳብ ያላቸውን ግለሰቦች የሚያገናኝ መረብ መሆኑም ተነግሯል።

በደምሰው በነበሩ