በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር በአሸባሪው ትሕነግ ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት ተመለከቱ

ጥር 13/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ በአሸባሪው የትሕነግ ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን ወሎ ዩኒቨርሲቲን እና ደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ተመለከቱ።
በቡድኑ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ጥገና ተደርጎለት በሚቀጥለው ወር የመማር ማስተማር ሥራውን በከፊል እንደሚጀምር ተገልጿል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት እና የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ዶክተር መንገሻ አየነ አሸባሪው ትሕነግ በተቋማቱ ላይ ያደረሰውን ጉዳት በአምባሳደሩ ለተመራው ልኡካን ቡድን ገለጻ አድርገዋል፡፡
አሸባሪ ቡድኑ በተቋማቱ ላይ የፈፀመው ጉዳትና ዝርፊያም ፈጥኖ ሥራ ለማስጀመር በማያስችል መልኩ መሆኑን ተናግረዋል።
አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው መልሶ እንዲቋቋም ድጋፍ እንደሚደረግ መግለጻቸውም ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪ በፈረንሳይ ካሉ አቻ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በማስተሳሰር የቴክኖሎጂና አሰራር ልምድ ልውውጥ እንዲደርግ ለማስቻል ቃል መግባባታቸውን ዶክተር መንገሻ ጠቅሰዋል።
ልኡኩ የተቋማቱን ጉዳት ተዘዋውሮ መመልክቱ የሽብር ቡድኑ ያደረሰውን ጥፋት ለዓለም ሕዝብ ለማሳወቅ እንዲሁም አንዳንድ ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃን የሽብር ቡድኑን በመደገፍ የሚያሰራጩትን የውሸት ዘገባ ለማጋለጥ የጎላ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ ተቋማትንና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ተቋሙን መልሶ ለማደራጀትና የመማር ማስተማር ሥራውን ለማስጀመር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር መንገሻ ተናግረዋል።
”በሚቀጥለው የካቲት ወር መጀመሪያ የሕክምና ተማሪዎችን ተቀብለን ትምህርት ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት እያደረግን ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ በወሩ መጨረሻ ደግሞ ሌሎች ነባር ተማሪዎችን እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚያስተምራቸው ከ26 ሺሕ በላይ ተማሪዎች እንደነበሩት የተቋሙን መረጃ ዋቢ አድርጎ ኢዜአ ዘግቧል።