በኢትዮ-ህንድ ኢንቨስትመንትና ንግድ ላይ ያተኮረ ፎረም ተካሄደ

የካቲት 21/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያን እና ህንድን በንግድ፣ ኢንቨስትምንት እና ቱሪዝም እድሎች ለማስተዋወቅ ያለመ የኢትዮ-ህንድ የኢንቨስትመንት ፎረም በበይነ መረብ ተካሂዷል።
ፎረሙ በህንድ ኢፌዴሪ ኤምባሲ ዘ ዲፕሎማቺቲስት መጽሔት ጋር በመተባባር የተዘጋጀ ሲሆን በህንድ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ እንዲሁም ከ45 በላይ የህንድ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል።
አምባሳደር ትዝታ የህንድ የንግዱ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋዩን እንዲያፈስ እና ቢዝነስ ለመሥራት ያለውን እድልና አቅም ለማስተዋወቅ ፎረሙ ጠቃሚ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ ለሚፈልጉ የውጭ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እያደረገ ያለውን ጥረት በተመለከተ ዝርዝር አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ በበኩላቸው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ አስቸጋሪ ወቅት እንኳን ወደ 35 የሚጠጉ የህንድ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንቨስትመንት ፍቃድ አግኝተዋል ብለዋል።
ይህ የሚያሳየውም ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሃብቶች ብዙ ያልተነካ እና ግዙፍ የኢንቨስትመንት አቅም እንዳላት ነው ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡