በኢንዱስትሪ ፓርኮች እያመረቱ ያሉ ኩባንያዎች የጃፓንን ሰፊ ገበያ እንዲጠቀሙ የሚያስችል ምክክር ተደረገ

 

ሰኔ 5/2016 (አዲስ ዋልታ) በኢንዱስትሪ ፓርኮች እያመረቱ የሚገኙ ዓለም አቀፍና ሀገር በቀል ኩባንያዎች አሁን ላይ ካላቸው ገበያ በተጨማሪ የጃፓንን ሰፊ ገበያ ለመጠቀም በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ምክክር ተደረገ።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ ጋር ውይይት አድርገዋል።

አምባሳደሩ በውይይታቸው ተጨማሪ የጃፓን ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በነፃ ንግድ ቀጣና ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ጃፓን ካላቸው ረጅምና ጠንካራ ወዳጅነት አንፃር የጃፓን ኢንቨስተሮች በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ያላቸው ተሳትፎና ድርሻ እንደሚጠበቀው አለመሆኑን ጠቁመዋል።

ተሳትፏቸውን ለማሳደግ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ለዚህም ኮርፖሬሽኑ ከምንግዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑን ለአምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ አንስተውላቸዋል።

በቅርቡ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ፓስፖርትን ጨምሮ ዓለም ዓቀፍ የደህንነት መስፈርቶችን የሚያሟሉ ሚስጥራዊ የህትመት ውጤቶችን የሚያመርት ቶፓን ግራቪቲ የተሰኘ ግዙፍ የጃፓን ኩባንያ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ መቀመጡ ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።