በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ ኩባንያዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት ያለመ ውይይት ተካሄደ

ኅዳር 21/2014 (ዋልታ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመሆን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ አምራች ባለሀብቶችን በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎችና ባለሀብቶቹ በገጠሟቸው የተለያዩ ችግሮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ውይይቱ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ሲያደርጉ የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ለመለየትና ለችግሮቹም መፍትሄ ለማስቀመጥ ያለመ ነው ብለዋል፡፡

አክለውም በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረጋችሁ እንዲሁም ኢትዮጵያ ላይ ባላችሁ የፀና እምነት ምስጋና ይገባችኋል ሲሉ ባለሀብቶቹን ማመስገናቸውን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሳንዶካን ደበበ በበኩላቸው ውጫዊ ጫናውም ሆነ ውስጣዊ ሁኔታው ሳይበግራቸው ምንም አይነት የምርትም ሆነ የሰራተኛ መቀነስ ሳይፈጠር በምርት ሂደታችው ላይ መገኘታችው በኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ህዝብ ላይ ያላችሁን እምነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሳንዶካን ደበበ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስራ አስኪያጆች፣ ከየኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የተወጣጡ አምራች ባለሀብቶችና ተወካዮቻቸው ተገኝተዋል፡፡