በኢፌዴሪ አየር ኃይል የደጀን አቪዬሽን ኢንዱስትሪ የማዕረግ እድገት ሰጠ

ጥቅምት 17/2014 (ዋልታ) በኢፌዴሪ አየር ኃይል የደጀን አቪዬሽን ኢንዱስትሪ የመቆያ ጊዜያቸውን ለሸፈኑና የተሻለ የሥራ አፈፃፀም ለነበራቸው መስመራዊ መኮንኖችና ባለሌላ ማዕረግተኞች የማዕረግ እድገት ተሰጠ።

ለተሿሚዎች የተፈቀደላቸውን ማዕረግ በማልበስ የሥራ መመሪያ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ አየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለሰው ኃብት ልማት ብርጋዴር ጄኔራል ይታያል ገላው፤ የማዕረግ እድገት ለበለጠ ኃላፊነት መታጨት ነው ብለዋል።

በመሆኑም አሁን ያለውን አገራዊ ሁኔታ በመረዳትና ወቅቱ የሚጠይቀውን አመራር በመስጠት ለበለጠ ተቋማዊ የለውጥ ስኬትና የግዳጅ አፈፃፀም ስኬታማነት መትጋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የማዕረግ እድገት የተሰጣቸው ተሿሚዎች በበኩላቸው በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የኅልውና አደጋ ሰራዊቱ በታላቅ ተጋድሎ እየቀለበሰና አኩሪ ድሎችንም እያበሰረ በሚገኝበት ሰዓት የማዕረግ እድገት ማግኘታቸን አስደስቶናል ብለዋል፡፡

በቀጣይም ማንኛውንም መስዋትነት በመክፈል ሕዝብና መንግሥት የሰጡትን ተልዕኮና ግዳጅ በብቃት እንደሚወጡ መግለፃቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል።