በእስራኤል ሀገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

ግንቦት 3/2014 (ዋልታ) በእስራኤል ሀገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ ምግብና አልባሳት ድጋፍ አደረጉ፡፡

በእስራኤል ሀገር በቤት ሼሜሽ ከተማ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን “ሰውን ለመርዳት የልብ ርቀት እንጂ የቦታ ርቀት አይገድበውም” በሚል መሪ ሃሳብ ድጋፍ ማድረጋቸውም ተገልጿል።

የድጋፉ አስተባባሪ ገብሬ ዋሴ የዋጋ ግምቱ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሆነ 303 ኩንታል ዱቄትና አልባሳት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ገንዘቡ በእስራኤል ሀገር ከሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን መሰብሰቡንም አስታውቀዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ አንተነህ ገብረ እግዚአብሄር በእስራኤል ለሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ተፈናቃዮች አሁንም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ገልጸው ሌሎችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል።