ነሃሴ 21/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ አስተባባሪነት በበይነ መረብ ውይይት ተካሄዷል፡፡
መድረክ ላይ የተሳተፉ በእስራኤል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሃገራቸውን ለመደገፍ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው ለመቀጠል ቃል ገብተዋል፡፡
በየኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት በእስራኤል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሃገራቸውን ለመደገፍ እያደረጉ ስላለው አስተዋጽኦ አመስግነው ዳያስፖራዎቹ ለሃገራዊ ፕሮጀክቶችም ሆነ ወቅታዊ ጥሪዎች የሚያደርጉት ድጋፍ ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንዲችል አደረጃጀቶችን እንዲጠቀሙ ጠይቀዋል።
በእስራኤል የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ረታ ዓለሙ በበኩላቸው÷ በእስራኤል ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ እንደሚገኝ ገልጸው ዳያስፖራው ለሃገሩ የሚያደርገው ድጋፍ በተቀናጀ መልኩ ስለማይመራ ከዳስፖራው ቁጥርና የማድረግ አቅም አንጻር ተጽዕኖ መፍጠር እንዳልተቻለ ገልጸዋል።
በእስራኤል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አደረጃጀት ተወካዮችም ለሃገራቸው የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠልና በተቀናጀ መልኩ መመራት እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡
ለዚህም ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርና ተጨማሪ ሀብትን ለማሰባሰብ በየአደረጃጀቶቻቸው ህዝቡን ማንቃትና መቀስቀስ እንዳለባቸው፣ አዳዲስ የሃብት ማሰባሰቢያ መንገዶችን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግና በግለሰብ ደረጃ ከሚደረግ ድጋፍ በተጨማሪም ተቋማትን በመቅረብ ትብብር መጠየቅ እንደሚገባ መግለፃቸውን ከዳያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡