በኦሮሚያ ተላልፎ የነበረው የሰዓት እላፊ መነሳቱ ተገለጸ

ኅዳር 9/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በሰውና በተሽከርካሪ ላይ ተላልፎ የነበረው የሰዓት እላፊ መነሳቱ ተገለጸ፡፡

የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ የተላለፈውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም በተመለከተ ግምገማ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

በዚህም በሰውና በተሽከርካሪ ላይ የተላለፈው የሰዓት እላፊ ገደብ በማህበረሰቡ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ጫናን እያሳደረ መሆኑን ከግምገማው የተገኘው ውጤት እንደሚያሳይ አንስቷል።

ይሄንንም ተከትሎ ህዝቡ ሰላሙን እየጠበቀ ስራውን እንዲሰራ ጥሪ በማስተላለፍ በሰዎችና ተሽከርካሪ ላይ ተላልፎ የነበረው የሰዓት እላፊ ከዛሬ ጀምሮ መነሳቱን ገልጿል።

ነገር ግን በየትኛውም ሰዓት አስፈላጊ ሆኖ ስገኝ ድንገተኛ ፍተሻ እንደሚደረግ እና ማህበረሰቡም በአካባቢው አስጊ የሆነ እንቅስቃሴ ሲመለከት ለሚመለከተው አካል መጠቆም እንደሚገባ የክልሉ ፍትህ ቢሮ በመግለጫው አሳስቧል።

ከኅዳር 3 ጀምሮ በክልሉ ከምሽት 3 ሰዓት እስከ ንጋት 11:30 ዜጎች እና ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርግ አዋጅ ተግባራዊ ተደርጎ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

በታምራት ደሊሌ