በኦሮሚያ ክልል በሩብ ዓመቱ የልማት ሥራዎች በትኩረት መሰራታቸው ተጠቆመ

ሚያዝያ 3/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ችግር ሳይበግር በ3ኛው ሩብ ዓመቱ የልማት ሥራዎች በትኩረት መሰራታቸው እና በየደረጃው የሕዝብ ተሳትፎ መጨመሩ ተገለጸ።

የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ በ3ኛ ሩብ ዓመት በእቅድ አፈፃፀም ግምገማ የታዩ ጠንካራ እና ደካማ ጉዳዮችን አንስተው የ2015 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እቅድ ዝግጅት ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በክልሉ በ3ኛ ሩብ ዓመት የእቅድ አፈፃፀም በርካታ እምርታዎች መመዝገባቸው የተገለፀ ሲሆን ከዚህ ቀደም የነበሩ በእቅድ ያለመመራት ክፍተቶችን በመቅረፍ በአፈፃፀም ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮች መፈታታቸው ተገልጿል።

በቀበሌ ደረጃና ከዚያ በታች ባሉ መዋቅሮች ጠንካራ የፓርቲና የመንግሥት መዋቅር አለመጠናከር፣ ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር፣ በፕሮጀክት አፈፃፀም እና የገቢ አሰባሰብ ላይ ክፍተት መኖር እንዲሁም እርስ በእርስ ለመተራረም የሚደረገው ጥረት ጠንካራ አለመሆን እንደ ክፍተት ተወስደዋል ተብሏል።

ቀጣይ የክልሉ አቅጣጫዎችን በተመለከተ በርካታ ሥራዎች ይካሄዳሉም ነው ያሉት ኃላፊው በመግለጫቸው፡፡

በሕዝብ ተሳትፎ ጠላትን ማጋለጥ፣ የጠላት አደረጃጀቶችን መመንጠር፣ የመንግሥት የእርሻ ልማቶችን ማሻሻል፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ምርትን ማጠናከር፣ ለአረንጓዴ አሻራ የችግኝ እና የቦታ ዝግጅት ማጠናከር እና ሌሎችም ይገኙበታል ብለዋል።

በ2015 እቅድ ዝግጅት ላይ ከወዲሁ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው የቀጣዩ ዓመት እቅድ ከ2014 ዓ.ም እቅድ በ50 በመቶ እድገት እንዲታቀድ እና እንዲተገበር ይሰራልም ተብሏል።

በቁምነገር አሕመድ