በኦሮሚያ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የእለት ደራሽ እርዳታ እየቀረበ መሆኑ ተገለጸ

የካቲት 18/2015 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል በ10 ዞኖች በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የእለት ደራሽ እርዳታ እየተደረገ መሆኑን የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ ሙስጠፋ ከድር ገለጹ፡፡

ኃላፊው በክልሉ የተከሰተውን ድርቅና እየተደረገ ያለውን ድጋፍ አስመልክቶ ዛሬ መገለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በክልሉ ደቡብ ምስራቅ አካባቢ ላለፉት ሦስት ዓመታት ገደማ በአምስት የዝናብ ወቅቶች ዝናብ ሳይዘንብ መቅረቱ ድርቁን እንዳባባሰው ገልጸዋል።

ቀደም ብሎ በ8 ዞኖች 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን የነበረው የእርዳታ ፈላጊ ዜጎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት በ10 ዞኖች ወደ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን ተናግረዋል፡፡

በቦረና ዞን ብቻ ለ867 ሺሕ ዜጎች የእለት ደራሽ እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው ባለፉት ወራት 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የሚገመት 465 ሺሕ ኩንታል የምግብ እህል መቅረቡንም ተናግረዋል።

በአሳንቲ ሀሰን