በኦሮሚያ ክልል አሸባሪው ሸኔ ት/ቤትን ጨምሮ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አወደመ

ሚያዝያ 28/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ ኮያ አካሌ ቀበሌ አሸባሪው የሸኔ ቡድን የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ጤና ተቋምን ጨምሮ ሌሎች የማኅበረሰብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማውደሙ ተነገረ።
የሽብር ቡድኑ በኩዩ ወረዳ ለአራት አመታት የአከባቢውን ማኅበረሰብ ለተለያየ እንግልትና መከራ ሲዳርግ መቆየቱ የተነገረ ሲሆን በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማፍረሱ ተገልጿል።
በኮዬ አካሌ ቀበሌም ባስከተለው ውድመት ምክንያት የአከባቢው ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለዋል ፤ ነዋሪዎችም የጤና ተቋማት በመውደማቸው ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገዋል።
የኩዩ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ተሾመ ቀነኒሳ ፤ ይህ አጥፊ ቡድን እያስከተለ የነበረው ውድመት ግልፅ ባለመደረጉ እየደረሰ የነበረው ጉዳት ለአራት አመታት ዘልቋል ብለዋል።
ይሁንና አሁን የፀጥታ ኃይሉ ከአከባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመናበብ እየሰሩ ባሉት ሥራ ብዙዎቹ በአጥፊው ቡድን ስር ወድቀው የነበሩ ቀበሌዎች ነፃ ማውጣት መቻሉን ለዋልታ ተናግረዋል።
በተቀናጀ መልኩ እየተወሰደ ባለው እርምጃም የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ አጥፊ ቡድኑ ከኅበረተሰቡ ሰርቆ የነበረውን በሬዎች፣ የምግብ እህልና ሌሎች ቁሶችንም ማስመለስ መቻሉንም ነው የገለጹልን።
በርካቶቹ የአሸባሪው ቡድን አባላትንም መማረክና መደምሰስ ተችሏል ብለዋል።
በታምራት ደለሊ