በኦሮሚያ ክልል ከመንግሥት የልማት ተቋማት 3.6 ቢሊየን ብር መሰብሰቡ ተገለፀ

ጥር 21/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል በመንግሥት ከሚመሩ ስድስት የልማት ተቋማት ላይ 4.8 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 3.6 ቢሊየን ብር መሰብሰቡ ተገለፀ። በዚህም የዕቅዱ 76 ከመቶ መሳካቱ ተመላክቷል።

በኦሮሚያ ምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የመንግሥት ሀብት አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ ግርማ አመንቴ ዛሬ ለሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ በመንግሥት አስተዳደርና የበጀት ወጪ ረገድ በሰድስት ወር ውስጥ በክልሉ 54.6 ቢሊየን ብር ወጪ መደረጉን ገልፀዋል።

በበጎ አድራጎትም ከክልሉ ሕዝብ ጉልበትና ሀብት የተገኘው ወደ ገንዘብ ሲሰላ 35.6 ቢሊየን ብር የሚሆን ገንዘብ መሰብሰቡንም ተናግረዋል።

በዚህም በክልሉ በበጀት እጥረት ምክንያት የተጓተተ አንድም የልማት ሥራ እንደሌለ ገልፀዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ሶስት አዳዲስ የልማት ተቋማት “ኦሮ ፍረሽ፣ ኢጃ ዲቨሎፐርና ጀብዱ ሜትር መቋቋማቸውም ተገልጿል።
በታምራት ደለሊ