በኦሮሚያ ክልል 14 ንፁሃን የተገደሉበትን የወንጀል ድርጊት እያጣራ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ አስታወቀ

ኮሚሽነር ግርማ ገላን

ጥር 26/2014 (ዋልታ) ኅዳር 24 በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ የተፈፀመውን ግድያ ተከትሎ የኦሮሚያ ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ገላን በሰጡት መግለጫ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ እስካሁን 2 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው በምርምራ ሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።

“ኅዳር 24 ቦሴት ወረዳ 14 ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል፤  ከአንድ ቀን በፊት ኅዳር 21 ለዘመቻ በተሰማሩ 11 የኦሮሚያ ፓሊሶች ላይ ግድያ ተፈፅሟል” ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ “እስካሁን ግድያውን ማን እና እንዴት እንደፈፀመው በመጣራት ላይ መሆኑን”ም ገልጸዋል።

በምርመራ ሂደቱ  መነሻ  የሆኑ እና የተለዩ ጉዳዮች መገኘታቸውንም ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኅዳር 24 የከረዩ አባገዳ ከድር ሀዋስ ቦሩ በአሸባሪው ሸኔ ቅጥረኛ መገደላቸውን ማሳወቁና ሀዘኑን መግለፁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ ምርምራ ሲያደርግ መክረሙን በመጥቅስ ትናንት ጥር 25 ባወጣው መግለጫ ግድያው በክልሉ የፀጥታ አባላት መፈፀሙን ገልፆ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው አካለት ለሕግ እንዲቀርቡ ሲል ጠይቋል።

ኮሚሽኑ “በከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ላይ ግድያ የፈጸሙና ያስፈጸሙ የፀጥታና የአስተዳደር አባላት ላይ ተገቢው የወንጀል ምርመራ ተደርጎ ለፍትሕ ሊቀርቡ ይገባል” ሲል ባወጣው መግለጫ ኅዳር 21/2014 ለሥራ ወደ ፈንታሌ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ሄደው ከቀኑ 8፡00 ሰዓት አከባቢ ወደ መተሃራ ከተማ በመመለስ ላይ የነበሩ የፀጥታ አባላት ላይ በወረዳው ሀሮ ቀርሳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ኢፍቱ በተባለ ቦታ ላይ ማንነታቸው ባልታወቀ የታጠቁ ኃይሎች በተፈጸመ ጥቃት የ11 ፖሊስ አባላት ህይወት ማለፉና ቢያንስ 17 ሌሎች የፖሊስ አባላት መቁሳለቸውን በምርምራ ጥናቴ አውቄያለሁ ብሏል።

“ይህንን ተከትሎ ኅዳር 22 ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ጥቃቱን ያደረሱ ተጠርጣሪዎችን ለመፈለግ በፈንታሌ ወረዳ ጡጢቲ ቀበሌ ልዩ ስሙ ዴዲቲ ካራ ከሚባል የከረዩ ሚችሌ አባገዳዎችና የጅላ አባላት የመኖሪያ ሰፈር የደረሱ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች 39 የጅላ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የዓይን እማኞች አስረድተዋል” ነው ያለው።

“በፀጥታ አባላት ቁጥጥር ስር የዋሉ የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት መካከል 16 ሰዎች ወደ ጨቢ አኖሌ ጫካ ተወስደው 14ቱ ሰዎች በጥይት ተመተው እንደተገደሉም” የሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽኑ አስረድቷል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ግን የወንጀሉን ተጠያቂዎች ማንነት ጨምሮ ጉዳዩ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን ነው በመግለጫው ያሳወቀው።

በማኅበራዊ ትስስር ገጾች እንደሚዘዋወረው ፖሊስ መመሪያ ሰጥቶ ንፁኃን ሰዎችን ሊያስገድል አይችልም ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ሕጉም የፖሊስ ስነ ምግባርም አይፈቅድም፣ የፖሊስ አባል ድርጊቱን ፈፅሞት ከሆነም በሕግ ይጠየቃል ብለዋል።

ፖሊስ ያገኘውን ጥቆማ አጣርቶ በሕግ ማስጠየቅ ሲችል ነው በጉዳዩ ላይ መብራሪያ የሚሰጠው በማለትም የኢሰመኮና ፖሊስን የአሰራር ሂድት ልዩነት አንስተዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽሩ አክለውም የኢሰመኮን መግለጫ አድሏዊነት የሌለበት፣ የሕዝብ ወገንተኝነትን የሚያሳይ ለፖሊስም አጋዥ የሆነ መግለጫ ነው ብለውታል፡፡

ከዚህ ቀደም 14ቱን ሰዎች ወይም የከረዩ አባገዳዎችን የገደለው ሸኔ ነው የሚል መረጃ የፖሊስ ኮሚሽኑ አላወጣም ከወጣም ስህተት ነው ብለዋል።

በተስፋዬ አባተ

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://www.facebook.com/waltainfo

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስላላችሁ እናመሰግናለን!