በኪንሻሳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዳግም ሊከፈት ነው

በ1980ዎቹ በበጀት እጥረት ተዘግቶ የነበረው ኪንሻሳ የኢትዮጵያን ኤምባሲ ዳግም ሊከፈት መሆኑ ተገለጸ፡፡

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ባደረጉት የሥራ ጉብኝት ከፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቺሴኬዲ ጋር በተለያዩ የሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ የኢትዮጵያን ኤምባሲ በኪንሻሳ መልሶ ለመክፈት መወሰኑን “ኪንሻሳ ተመልሰናል” በማለት አስታውቀዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1962 ተከፍቶ የነበረው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ መጀመሪያ በበጀት እጥረት ምክኒያት ተዘግቶ እንደነበረ ይታወሳል፡፡

ሁለቱ አገሮች በአቪየሽን ዘርፍ ስምምነት ያላቸው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ወደ ኪንሻሳ፣ ሉቡምባሺና ጎማ ከተሞች ይበራል፡፡

ፕሬዚዳንት ቺሴኬዲ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበርነትን በመጪው ሳምንት ከደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት እንደሚረከቡ ይታወቃል፡፡

በመሆኑም የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው መርህ መሰረት የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሹን ውይይት በአደራዳሪነት ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ስላካሄደዉ የህግ ማስከበር ዘመቻ፣ አሁን እየተሰራ ስላለው በተለይም የመልሶ ማቋቋምና የሰብዓዊ እርዳታ ገለጻ ማድረጋቸውን የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡