ግንቦት 23/2013 (ዋልታ) – በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮ – ካናዳውያን የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የጣለውን የጉዞና ተያያዥ ማዕቀብ በመቃወም በካልጋሪ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ፡፡
በካናዳ አልበርታ ግዛት በካልጋሪ፣ ሌትብሪጅና ፎርትማክመሪ የሚኖሩ ኢትዮ – ካናዳውያን የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የጣለውን የጉዞና ተያያዥ ማዕቀብ በመቃወም በካልጋሪ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ፡፡
ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ በትግራይ ክልል አሸባሪው ህወሃት በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊታ ላይ ያደረሰውን ኢሰብዓዊ ጭፍጨፋ ተከትሎ መንግስት የወሰደውን የህግ ማስከበርና ወንጀለኞቹን ለህግ የማቅረብ ህጋዊ እርምጃ የሚደግፉ መሆናቸውን ገልጸው፣ ሆኖም ይህን ክስተት ተከትሎ የአሜሪካን መንግስት እውነታውን በትክክል ሳይመረምር በተሳሳተና እውነትን መሰረት ባላደረግ ሁኔታ የኢትዮጵያን መንግስት ከአሸባሪዎች እኩል በመመልከት ማዕቀብ መጣሉ ስህተት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ሰልፈኞቹ በመልዕክታቸው ወቅቱ ሃገራችን ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ የዜጎቿን ድጋፍ የምትፈልግበት ጊዜ መሆኑን፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለምንም የሃይማኖት፣ የብሔርና የፆታ ልዩነት በአንድነት በመቆም ድጋፉን ማድረግ እንዳለበት፣ አሜሪካም ሆኑ ሌሎች ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ የሚፈልጉት ሃገሪቱ ደሃ በመሆኗ መሆኑን፣ መንግስት ሃገሪቱዋን ከድህነት ለማውጣት የሚያደርገውን ጥረት በተለያየ መንገድ እንደሚደግፉና ከዚህ ጋር ተያይዞ ወደ ኢትዮጵያ የሚልኩትን ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ብቻ እንደሚልኩ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተያዘለበት ፕሮግራም መሰረት ሙሌቱ እንዲካሄድና ፕሮጄክቱም እንዲጠናቀቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ፣ በተመሳሳይ የሃገራቸው የካናዳ መንግስትም በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ መሰረት እንዲይዝ እንዲደግፍና አላስፈላጊ ጫና ኢትዮጵያ ላይ ከማሳረፍ እንዲቆጠብ ጠይቀዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ ከወጣት እስከ አዋቂ የተሳተፉ ሲሆን፣ የተለያዩ መልዕክቶችም በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ቀርበዋል፡፡
በመጨረሻም ሰልፈኞቹ በሃገራቸው ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው ጫና እስካልቆመ ድረስ ተመሳሳይ ዝግጅቶችን በሰፊው ለመቀጠልና ለኢትዮጵያ ህዝብ ድምጽ ለመሆን ቃል በመግባት ፕሮግራማቸውን ማጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲን ጠቅሶ ኢፕድ ዘግቧል።