በክልሉ ሰላምን ለማረጋገጥ ሕዝቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

ሚያዝያ 12/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል ሰላምን ከማረጋገጥ አንፃር ሕዝቡ እያደረገ የሚገኘውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ጠየቀ፡፡

በክልሉ የፋሲካ በዓልን ጨምሮ በቀጣይ የሚከበሩ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል፡፡

የሀረሪ ክልል ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን ዋደራ የፋሲካ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ከማስቻል አንፃር ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የኢድ አልፈጥር እና በክልሉ በልዩ ሁኔታ የሚከበረውን የሸዋል ኢድ በዓላት ካለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበሩ እና ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶችም የተሳካ ቆይታ እንዲያደርጉም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዚህም የክልሉ የፀጥታ ኃይል፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የአገር መከላከያ ሰራዊት እና የኦሮሚያ ልዩ ኃይልን ያካተተ ግብርኃይል መቋቋሙን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡