በክልሉ በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ

የካቲት 23/2014 (ዋልታ) በደቡብ ክልል በትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በልዩ ትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

በክልሉ የ2014 ዓ.ም የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም የትምህርት ጉባኤ በጂንካ ከተማ እየተካሔደ ነው፡፡

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) በክልሉ በትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በልዩ ትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።

በክልሉ በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እየራቁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤቶችን ማዘጋጀት መቻሉንም ጠቁመዋል።

የቅድመ አንደኛ ደረጃ ተደራሽነት ላይ ትኩረት በመስጠት መሰራት አለበት ያሉት ኃላፊው በተመረጡ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራምን ማጠናከር እንደሚገባም አብራርተዋል።

በክልሉ የትምህርት ጥራት ችግር መኖሩን ለኅብረተሰቡ በግልጽ ማሳወቅ ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል።