በክልሉ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 80 ሺሕ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ተገለጸ

ሰኔ 17/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል 80 ሺሕ ወጣቶች የሚሳተፉበት የዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርኃ ግብርን ለማከናወን ዝግጅት ማጠናቀቁን የክልሉ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳዮች ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ኃላፊ ደሊላ ዩሱፍ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ ተጨባጭ ውጤት ያመጡ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በዘንድሮው ዓመትም የታዩ መልካም ተሞክሮዎችን በማጎልበትና ክፍተቶችን በመቅረፍ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን በሚያስችል መልኩ ዝግጅት መጠናቀቁን አስረድተዋል።

በዚህም በክልሉ 80 ሺሕ ወጣቶችን ያሳተፈ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚከናወን ነው ኃላፊዋ የገለፁት።

በመርኃ ግብሩም የ100 አቅመ ደካማ ወገኖች ቤት የማደስ ሥራን ጨምሮ የአረንጓዴ አሻራ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት፣ ደም የመለገስ እና የከተማ ግብርና ሥራዎች እንደሚከናወኑ አብራርተዋል።

ከሰኔ 22 ቀን ጀምሮ ለሁለት ወራት የሚከናወነው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በገንዘብ ሲተመን ከ5 ሚሊየን ብር በላይ እንደሚገመት ተናግረዋል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)