በክልሉ በድርቅ ለሚጠቁ አካባቢዎች የሚውል ከ73 በላይ ግድቦች በግንባታ ላይ መሆናቸው ተገለጸ

መጋቢት 27/2015 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል በድርቅ ለሚጠቁ አካባቢዎች የሚውል ከ73 በላይ ግድቦች በግንባታ ላይ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

ግንባታው ከ30 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበትና በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ተመላክቷል።

የፕሮጀክቱ አካል የሆነው በቦረና ዞን አሬሮ ወረዳ እየተገነባ ያለው ግድብም ከ2 ነጥብ 5 ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዙ የተገለጸ ሲሆን ግድቡ ሲጠናቀቅ 17 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ እንደሚይዝ የኦሮሚያ ክልል መስኖና አርብቶ አደሮች ቢሮ ገልጿል።

ቢሮው አክሎም ግድቡ ተጠናቆ አገልግሎት ላይ ሲውል ከ2 ሺሕ በላይ አባዎራዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

በዞኑ በግንባታ ላይ ካሉ 14 ፕሮጀክቶች ውስጥ ግንባታቸው 90 በመቶ የደረሰ ሲሆን ሰኔ 2015 ዓ.ም ግንባታቸውን አጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩም ተገልጿል።

ግድቦቹ ሲጠናቀቂ ለመጠጥ፣ ለአሳ ምርት፣ ለመስኖና ለቱሪዝም ይውላሉም ተብሏል።

በዙፋን አምባቸው