የካቲት 7/2015 (ዋልታ) በሶማሌ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ገለጹ።
ለሁለት ቀናት በጅግጅጋ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ተጠናቋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በግማሽ ዓመቱ የተከናወኑ አበይት ተግባራትን በሚመለከት ሪፖርት አቅርበዋል።
በተለይም ከሰላምና ፀጥታ ጋር በተያያዘ የአልሻባብን ስጋት ለመቀነስ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው በዚህም ቡድኑ በክልሉ ሊያደርስ አቅዶ የነበረውን የሽብር ተግባር ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።
በግብርናው ዘርፍ በግማሸ ዓመቱ 655 ሺሕ ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 20 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉንም ተናግረዋል።
በግማሽ አመቱ በክልሉ 4 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ በመሰብሰብ የእቅዱን 99 በመቶ ማሳካት መቻሉ የተጠቆመ ሲሆን ለ52 ሺሕ 919 ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ተብሏል።
ባለፉት 6 ወራት በክልሉ 5 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 2 መቶ 11 ኢንቨስተሮችን ማስተናገድ መቻሉን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ባቀረቡት ሪፖርት የገለፁት።
የቀረበው ሪፖርትም በምክር ቤቱ አባላት በሰፊው ውይይት ተደርጎበት ፀድቋል።
የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አያን አብዲ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የአስፈፃሚ አካላት ስራዎችን ከመከታተልና ከመደገፍ አንፃር እያከናወኑት የሚገኘውን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር ቅርንጫፍ)