በክልሉ ከማዕድን ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግና ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሠራ ተገለጸ

ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) በክልሉ ከማዕድን ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግና ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሠራ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።

በኢፌዴሪ ማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ሚሊዮን ማቴዎስ የተመራ ልዑክ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በማዕድን ዘርፍ በትብብርና በቅንጅት ለመሥራት በቦንጋ ከተማ የምክክር አካሂደዋል።

በምክክር መድረኩ የተገኙት ሚኒስትር ዴኤታው የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ደጀን የሆነውን የማዕድን  ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሚኒስቴሩ ከክልሉ መንግስት ጋር በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ ለክልሉ ማዕድን ቢሮ የዘርፉን ስራ ለማጠናከር አንድ መኪና፣ የኮምፒውተርና ኤሌትሮኒክስ ድጋፍ አበርክቷል። በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

በተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በክልሉ ማዕድን ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግና ኅብረተሰቡም ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የማዕድን ዘርፍ በሚገኝባቸው አካባቢዎች የሠላምና የጸጥታ ሁኔታውን ለማረጋገጥ የክልሉ መንግስት ከፌደራል መንግስት ጋር በቅንጅትና በመደጋገፍ እንደሚሠራ  መናገራቸውን ከክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡