በክልሉ ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን ለማስወገድ የሚያስችል ግብርሃይል ተቋቋመ

ሚያዚያ 19/2013 (ዋልታ) – በአፋር ክልል ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን ለማስወገድ የሚያስችል ግብርሃይል መቋቋሙን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጣሃ አሊ ለዋልታ እንደገለጹት፣ ከጸጥታ አካላት፣ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ እንዲሁም ከሀገር ሽማግሌዎች የተወጣጡ አካላት የተሳተፉበት ግብርሃይል ነው የተቋቋመው፡፡

በምርጫ ወቅት በተለይ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለማስቀረት እና ነጻ ምርጫ ለማካሄድ ሴቶች የተሳተፉበት ግብርሃይል መቋቋሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ከምርጫ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል ያስችላል የተባለው ግብርሃይሉ 15 አባላት የተካተቱበት ሲሆን፣ በተቀናጀ መልኩ መረጃዎችን በቅርበት በመከታተል ለችግሮች መፍትሔ እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ግብርሃይሉ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሮችን ለመቆጣጠር እንደሚሰራ እና የሚፈጠሩ ችግሮችንና መፍትሔዎቻቸውን ሰንዶ በማስቀመጥ ለቀጣይ ምርጫ መማሪያ እና ግብዓት ለማድረግ በሶፍት ዌር ታግዞ እንደሚሰራ አቶ ጣሃ አሊ ገልጸዋል፡፡

(በብርሃኑ አበራ)