በክልሉ ከ91 ሺሕ ኩንታል በላይ የቦቆሎ እና ከ40 ሺሕ ኩንታል በላይ የስንዴ ዘር እየተሰራጨ ነው

ሚያዝያ 26/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል ለመኸር እርሻ 91 ሺሕ 776 ኩንታል የቦቆሎ እና 40 ሺሕ 687 ኩንታል የስንዴ ዘር ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑ ተገለፀ፡፡

የክልሉ የግብርና ጥራትና ደኅንነት ባለስልጣን ለ2014/2015 ዓ.ም የመኸር እርሻ በዋና ዋና የሰብል ዓይነቶች በቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍ፣ የቢራ ገብስ እና ሌሎችም እንደተፈላጊነታቸው በላቦራቶሪ ፈትሾ የጥራት ደረጃ ያሟላ ዘር በግብርና ቢሮ በኩል ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሞላ ካሳ ለ2014/2015 ዓ.ም የመኸር እርሻ የሚሆን ምርጥ ዘር ከምርጥ ዘር አባዥ ድርጅቶች ዩኒየኖች፣ ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ የግብርና ምርምር ማዕከላትና ዩኒቨርሲቲዎች የጥራት ቁጥጥር በማድረግ እያዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመት ለመኸር እርሻ 91 ሺሕ 776 ኩንታል የቦቆሎ እና 40 ሺሕ 687 ኩንታል የስንዴ ዘር በላቦራቶሪ ተፈትሾ የጥራት ደረጃ ያሟላ እና መለያ ምልክት ተሰጥቶ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑን ተናግረው ተመሳስለው ገበያ ላይ ከሚሸጡ የጥራት ቁጥጥር ባልተደረገበት ዘር እንዳይታለሉ አሳስቧል፡፡

በሌላ በኩል ለመኸር እርሻ የሚሆን ሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ በሀገር ዐቀፍ ደረጃ እጥረት መከሰቱን ተከትሎ ‹‹ኢኮ ግሪን›› የተሰኘ ፈሳሽ ማዳበሪያ በአማራጭነት በግብርና ሚኒስቴር እውቅና የተሰጠው በመሆኑ አርሶ አደሩ ከኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ከእርሻ አገልግሎት ማዕከላት ብቻ በመግዛት መጠቀም እንደሚችሉ መናገራቸውን ከአማራ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW