በክልሉ ውድመት አድርሰዋል የተባሉ 16 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ግንቦት 13/2014 (ዋልታ) በዘረፋና ሥርቆት ተሰማርተው በሕዝብና መንግሥት ሀብትና ንብረት ላይ የውድመት አደጋ አድርሰዋል ተባሉ 16 ተጠርጣዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሶማሌ ክልል ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር መሀሙድ ሼክ አህመድ እንደገለጹት በጅግጅጋ ከተማ በዘረፋና ሥርቆት ተሰማርተው በሕዝብና መንግሥት ንብረት ላይ የውድመት አደጋ አድርሰዋል የተባሉ 16 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ተጠርጣሪዎቹ የኢትዮ-ቴሌኮም የቴሌ-ኮሙዩኒኬሽን መሳሪያዎች፣ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል የመስመር ገመዶች እንዲሁም ለጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲና ጅግጅጋ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ከሚሰጡት የውሃ ጉድጓዶች አንዱ የሆነውና “ቡሮቆየር” ተብሎ የሚታወቀውን ውሃ ጉድጓድ መሳሪያዎች ለሥርቆትና መበጣጠስ አደጋ የማጋለጥ ወንጀል የተጠረጠሩ መሆናቸውን ረዳት ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።

ሕዝቡ በመሰረተ ልማት አውታሮችና አገልግሎቶች ላይ ለአደጋና ሥርቆት የሚያጋልጡ አካላትን እንዲያጋልጥና ከጸጥታ አካላት ጎን እንዲቆም ረዳት ኮሚሽነር መሀሙድ ሼክ አህመድ ጥሪ ማቅረባቸውን የክልሉ ኮዩሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW