በክልሉ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ተጠየቀ

ግንቦት 29/2014 (ዋልታ) በክልሉ ተጠያቂነትን ለማስፈንና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የሀረሪ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጠየቀ።

የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ቢሮ ኃላፊ አዩብ አሕመድ በክልሉ ተጠያቂነትን ከማስፈንና የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አንፃር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተፈፀሙ የተለያዩ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ከ840 በላይ መዝገቦች ክስ መመስረቱን ጠቁመው በዚህም በ462 መዝገቦች ወንጀለኞች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ መወሰኑን ጠቁመዋል፡፡

በመንግሥት ከፍተኛ ፕሮጀክቶች፣ በመሬት እና በገቢ፣ በግዢ፣ በፍትሕና ፀጥታ ዘርፍ ላይ የሚስተዋሉ የሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በማጣራት በ19 ባለሙያዎች እና አመራሮች ላይ ክስ መከፈቱንና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በታክስ ስወራ እና ከሊዝ ጋር ተያይዞ 24 ሚሊየን ብር ለመንግሥት ገቢ መደረጉን ተናግረዋል፡።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ ወንጀሎች 2 ሺሕ 681 መዝገብ ላይ ክስ ተከፍቶ በፍርድ ቤት ማስቀጣት መቻሉን ጠቁመው በ81 መዝገቦችም ከ230 ሚሊየን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ኅብረተሰቡ በፍትሕ ሥርዓቱ እና በፀጥታ ዘርፍ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠትም ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በዚህም በተለይ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የሚፈፀሙ የሕግ ጥሰቶችና ወንጀሎችን የመቆጣጠር፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን የመከላከል እና የኑሮ ውድነትን እንዲባባስ የሚያደርጉ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ሥራም በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ኅብረተሰቡ እና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በክልሉ የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥና ተጠያቂነትን ለማስፈን እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)