በክልሉ የተፋሰስ አከባቢዎች ልማት ስራ በ3.2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንደሚካሄድ ተገለጸ

የተፋሰስ አከባቢዎች ልማት ስራ

ጥር 15/2015 (ዋልታ) በክልሉ የተፋሰስ አከባቢዎች ልማት ስራ በ3.2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንደሚካሄድ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ጌቱ ገመቹ በባሌ ዞን ሀረና ወረዳ ሻዌቲ ቀበሌ የተፋሰስ አከባቢዎችን ልማት ስራ አስጀምረዋል።

በክልሉ የተፋሰስ አከባቢዎች ልማት ስራ በ3.2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ እንደሚሰራና ከዛሬ ጀምሮ ለ60 ቀናት እንደሚቆይ ተናግረዋል።

የልማት ስራው በህብረተሰቡ ተሳትፎ እና በዜግነት አገልግሎት እንደሚሰራ የተናገሩት ኃላፊው የልማት ስራው የአፈር መሸርሸር፣ የተፈጥሮ ሀብትን ወደ ቦታው ለመመለስ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር እንደሚረዳ ገልጸዋል።

በክልሉ በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጸው ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ፌናን ንጉሤ (ከባሌ ዞን)