በክልሉ 6 ሺሕ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሊገነቡ ነው

ሰኔ 3/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል በዜግነት አገልግሎት ፕሮግራም 6 ሺሕ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገነቡ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ከ7 ሺሕ በላይ በሚሆኑ ቀበሌዎች ይከናወናል ተብሏል።

በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦራ ወረዳና በምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ከተማ የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ተካሂዷል።

ፕሮጀክቶቹ በክልሉ ያልነበረውን ቅድመ መደበኛ ትምህርት በመገንባት ጥራት ያለውን ትምህርት ለዜጎች ለማድረስ በዜግነት አገልግሎት ፕሮግራም በመታገዝ በ30 ቢሊዮን ብር ይገነባሉ ተብሏል።

ከሚያስፈልገው 12 ሺሕ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች 6 ሺሕ የሚሆነውን በዚህ ክረምት ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሠራ ተገልጿል።

እስከ አሁን በተሠራው ሥራ በ3 ሺሕ 11 ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሕጻናትን ተጠቃሚ አድርጓል።

መጪውን ትውልድ ለመቅረጽ የቢሮው ሠራተኞች የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለፕሮጀክቱ ስኬት አበርክተዋል።

በአሳንቲ ሀሰን