በክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 7.5 ቢሊየን ችግኞችን መትከል ችለናል – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

መስከረም 7/2016 (አዲስ ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች መተከሉን ገለጹ።

የኢትዮጵያዊያን ብርቱ እጆች በጽናት ታሪክ መስራት ቀጥለዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ በተጠናቀቀው የክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር ካቀድነው በላይ አሳክተን 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን መትከል ችለናል ብለዋል፡፡

የሁለተኛው ምዕራፍ የመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ማጠቃለያ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና የክልል ቢሮ ኃላፊዎች በተገኙበት በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

በማጠቃለያ መርኃግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር በ2015 የክረምት ወቅት ህዝቡን በነቂስ በማሳተፍ የተተገበረው የሁለተኛ ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከዕቅድ በላይ መፈጸም የተቻለ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ በዘንድሮ ዓመት በተካሄደው የችግኝ ተከላ ዘመቻ ወደ 7.5 ቢሊዮን ችግኝ መትከል መቻሉን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2ኛው ምዕራፍ ለመትከል የታቀደውን 50 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል ግብ በላቀ አፈፃፀም ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ህዝባችን ያሳየውን ትጋትና እና ብርታት መንግስት በእጀጉ ያከብራል ሲሉም አክለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ላለፉት አምስት ዓመታት በዘላቂነት በተተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 35 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል የተቻለበት በመሆኑ ሌሎች ሀገራትም የዘመቻውን በጎነት በመገንዘብ ተግባራዊ እያደረጉት ይገኛሉ።

በደረሰ አማረ