በክፍለ ከተማው የተለያዩ የመስሪያ ቦታዎች ለተጠቃሚዎች በዕጣ ተላለፉ

ኅዳር 15/2015 (ዋልታ) የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የተለያዩ የመስሪያ ቦታዎችን ለተጠቃሚዎች በዕጣ አስተላለፈ፡፡

ቢሮው ከዚህ በፊት በተለያየ ምክንያት አገልግሎት ያልሰጡ፣ በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ እና ለተጠቃሚ ተላልፈው ለአምስት ዓመታት አገልግሎት የሰጡ የመስሪያ ቦታዎችን ለተጠቃሚዎች ማስተላለፉን ነው ያስታወቀው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ መዲናዋ በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች የሚገኙባት እንደመሆኗ መንግስት ስትራቴጂ በመንደፍ የመስሪያ ቦታዎችን ገንብቶ ማስተላለፍን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል::

በዚህም 102 ኢንተርፕራይዞች እና 450 አንቀሳቃሾች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው ከዚህ ውስጥም 55 በመቶ የሚሆኑት ተጠቃሚዎች ሴቶች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን፣ የአካል ጉዳተኞች እና ከስደት ተመላሾች በዕጣው መካተታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ኢንተርፕራይዞች የሚወስዱትን የመስሪያ ቦታ ከህገ-ወጥ ድርጊት በመቆጠብ በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ማሳሰባቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW