በኮማንደር አትሌት ደራርቱ ስም የተሰየመ አደባባይ ምረቃ

መስከረም 10/2014 (ዋልታ) በኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ስም የተሰየመው አደባባይ የፊታችን እሁድ እንደሚመረቅ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌደሬሽንና የለሚ ኩራ ክፍል ከተማ አስታወቁ።

የመዲናዋ አትሌቲክስ ፌደሬሽንና የክፍለ ከተማው አመራሮች በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ በአፍሪካ የመጀሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት ሴት የኦሊምፒክ ባለድል በመሆን የበርካታ አትሌቶች የጀግንነት ምሳሌ ለሆነችው ኮማንደር አትሌት ደራርቱ አደባባይ መሰየሙ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አሊያስ ሙሀመድ፤ በጀግናዋ አትሌት ስም በክፍለ ከተማችን አደባባይ በመሰየሙ እንኮራለን ብለዋል።

እንደ ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ አይነት ዓለም አቀፍ ጀግኖችን ማክበር ሌሎች ጀግኖችን ለማፍራት ያግዛልም ብለዋል።

በመሆኑም በጀግናዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ስም የተሰየመው አያት አካባቢ የሚገኘው አደባባይ የፊታችን እሁድ በይፋ እንደሚመረቅ ገልጸዋል።

ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ተሉ እ.ኤ.አ በ1992 የባርሴሌና ኦሊምፒክም በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት ለሴት ጥቁር አፍሪካዊያን ፈር ቀዳጅ አትሌት ናት።

በሲዲኒ ኦሊምፒክም ለኢትዮጵያ ወርቅ አምጥታለች፤ ከዚህም ባለፈ በርካታ ድሎችን በማስመዝገብ ስሟ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ ይጠራል።

በእለቱ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ለማድረግ ዓላማ ያደረገ የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር እንደሚካሄድ የኢዜአ ዘገባ ያሳያል።