በኮሪያ ልሳነ ምድር እየተካሄደ ያለው ጥምር ወታደራዊ ልምምድ በኮርያ ልሳነ ምድር ውጥረትን አንግሷል

ነሐሴ 17/2014 (ዋልታ) አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ መጠነ ሰፊ የተባለለትን ወታደራዊ የመስክ ልምምድ በኮሪያ ልሳነ ምድር ማካሄድ መጀመራቸው ተነገረ፡፡ ልምምዱ በኮርያ ልሳነ ምድር ውጥረትን ፈጥሯል፡፡

ኡልቺ ፍሪደም ሺልድ ተብሎ የተሰየመው ልምምዱ በኮምፒውተር ሲሙሌሽን (በኮምቲውተር የታገዘ ምናባዊ እውነታ) ላይ የተመሰረተ የኮማንድ ፖስት ስልጠና፣ የመስክ እንቅስቃሴ እና የሲቪል መከላከያ ልምምዶችን በማጣመር የሚካሄድ መሆኑን የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ሺን ቤኦምቹል በጉዳዩ ላይ ሰሜን ኮሪያን ትቃወማለች ብሎ ማሰብ ፍትሃዊ እንዳልሆነ እና ጥምር ጦሩ ወደፊት በሰሜን ኮርያ ላይ ለሚወስደው ወታደራዊ እርምጃ ተጠያቂ መሆን እንደማይችል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ስልጠናው የሁለት ሀገራት ወታደሮች አንድ ሀገርን ለመከላከል ተስማምተው የሚሰሩበት ሲሆን የዛሬ 70 ዓመታት ገደማ ያለ ሰላም ስምምነት የኮሪያ ጦርነት ካበቃ በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ ለደቡብ ኮሪያ የምታደርገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ቁርጠኝነት ማሳያም ነው ተብሎለታል፡፡
የሀገራቱ አየር ኃይል ፣ የባህር ኃይል፣ የኅዋ እና የሳይበር ኦፕሬሽን በማቀናጀት እየተካሄደ ያለ ወታደራዊ ልምምድ ነው፡፡
በአንጻሩ ሰሜን ኮሪያ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ በዚህ ዓመት በርካታ ሚሳኤሎችን ሙከራ ያካሄደች ሲሆን የጦር መሳሪያዋም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቀቀ በመምጣቱ ኢላማቸውን ለመምታት የቻሉ መሆናቸውም ይነገራል፡፡
ጠላትን ለማንበርከክ ኒውክሌር እስከ መጠቀም እደርሳለሁ የሚሉት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ እያደረጉት ያለው መጠነ ሰፊ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ የኮሪያን ልሳነ ምድር ወደ ጦርነት አፋፍ እየወሰደው ነው ሲሉ ከሰዋል።
ደቡብ ኮሪያ የራሷ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ የላትም። አስፈላጊ ከሆነ የአሜሪካን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ተጠቅማ ከጠላት እራሷን እንደምትከላከል ግን ከስምምነት ላይ ደርሳለች፡፡