በኮርያ መንግስት ድጋፍ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማበልፀጊያ ማዕከል ሊቋቋም ነው

መጋቢት 17/2014 (ዋልታ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የኮርያ አለም አቀፍ ኮኦፕሬሽን ኤጀንሲ በአይሲቲ ፓርክ ውስጥ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራ ማበልፀጊያ ማዕከል ግንባታና ድጋፍ ዙሪያ መክረዋል።

ማዕከሉ በኮርያ መንግስት ድጋፍ በ6 መቶ ሺ ዶላር ወጪ በአይ ሲ ቲ ፓርክ ውስጥ የሚገነባ ሲሆን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤቶች የፈጠራ ስራዎቻቸውን የሚያበለፅጉበትና ወደ ንግድ የሚለውጡበት ነው ተብሏል።

በኮርያ አለም አቀፍ ኮኦፐሬሽን ኤጀንሲ ድጋፍ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እስከ 2025 የሚቆይ የ10 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት ተቀርፆ እየተተገበረ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ፒ ኤች ዲ) በዚህ ፕሮጀክት እየተደገፉ ያሉና ተወዳድረው ለተመረጡ 10 ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች እስከ 5ሺ ዶላር የሚደርስ የመነሻ ገንዘብ ተሰጥቷቸው በቅርቡ ይመረቃሉ ብለዋል።

የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራ ያላቸው ዜጎች በቀላሉ ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ ላይ እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የኮርያ መንግስት እያደረገው ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኮይካ የኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ  ሺንያንግ ሊ የኮርያ መንግስት በኢትዮጵያ የፈጠራ ስራ እንዲዳብር ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የዲዛይን ስራው የተጠናቀቀው ማዕከሉ በአይ ሲ ቲ ፓርክ ውስጥ የሚቋቋም ሲሆን የውስጥ እድሳት ስራ፣  የፈጠራ የንድፍ ስራ መሳሪያዎች፣ ባለሙያዎች እና አስፈላጊ መሳሪያዎች ይሟሉለታል ተብሏል።

ከልማት ባንክ እና ከተባበሩት መንግስታት ልማት ድርጅት ጋር በጋራ በተዘጋጀው የጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች የብድር ዋስትና ላይ መክረዋል።

በተባበሩት መንግስታት የኢኖቬሽን ልማት ፕሮጀክት ማዕቀፍ ላይ ትኩረት እንዲሰጠው አቅጣጫ መቀመጡን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።