መጋቢት 29/2014 (ዋልታ) በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ከ12 በላይ የጅምላ ጭፍጨፋ የተፈፀመባቸው ስፍራዎችና የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡
ዩኒቨርሲቲው በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ላለፉት 30 ዓመታት ሲፈፀሙ የነበሩ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን መነሻ አድርጎ ያካሄደውን ጥናት የመጀመሪያ ውጤት መግለጫ ሰጥቷል።
ጥናቱ እንዲካሄድ መነሻ የሆኑት አሸባሪው ትሕነግ በ1984 በጉልበት ወደ ትግራይ ክልል ባጠቃለለው የወልቃይት ጠገዴና አካባቢዎቹ የሚነሱ የማንነት ጥያቄዎችን የሚመልሰው በአፈና፣ እስራትና ግድያ ስለነበር መሆኑ ተነስቷል።
የሽብር ቡድኑ በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ፈፅሞ ጦርነት ከከፈተ ከ6 ቀን በኋላ ጥቅምት 30/2013 በማይካድራ ከ1 ሺሕ በላይ አማራዎችን በጅምላ መጨፍጨፉም አንዱ የጥናቱ መነሻ ነው ተብሏል።
ከተለያዩ ሙያዎች በተውጣጡ 21 የጥናት ቡድን አባላት ለ1 ዓመት ከ3 ወር የተካሄደውና አሁንም የቀጠለው ጥናት በአካባቢዎቹ ማንነትን መሰረት ያደረገ የጅምላ ግድያ መፈፀሙን ያረጋገጡ ማስረጃዎች ማግኘቱ ተገልጿል።
በዚህም ከ12 በላይ የጅምላ ጭፍጨፋ የተፈፀመባቸው ስፍራዎችና የጅምላ መቃብሮች የተገኙ ሲሆን የጅምላ መቃብር ስፍራዎቹ በስውር ቦታ መሆናቸው ተጠቅሷል። ገሃነም የተሰኘው የጅምላ መቃብር ቦታ ከሁሉም የከፋው ነው ያለው ጥናቱ በደርዘን የሚቆጠሩ የጅምላ መቃብርና የግፍ ማጎሪያዎችን የያዘ መሆኑንም አሳውቋል።
ትሕነግ ስውር ያላቸውን ቦታዎች ቢጠቀምም ታፍኖ የቆየው የአካባቢው ነዋሪዎችና ቀደም ሲልም ከትሕነግ ጋር ሲሰሩ የነበሩ ሰዎች በየመቃብሮቹ እነማን እና ምን ያህል ሰው በጅምላ እየተረሸኑና እንደተቀበሩ ለጥናት ቡድኑ ማሳወቃቸው ተገልጿል።
አሸባሪው ትሕነግ አካባቢዎቹን ሲገዛ በነበረባቸው ዓመታት በአካባቢዎቹ አማርኛ ቋንቋ መናገርን እንደወንጀል አድርጎ ይገድል፣ ያስርና ያፈናቅል እንደነበርም አጥኝዎቹ አሳውቀዋል።
ውጤቱን መነሻ አድርጎ መንግሥትና ሌሎችም አጋሮች ተጠያቂነትን እንዲያሰፍን፤ ውጤቱም በማስረጃዎቹ ተሰንዶ በሙዚየምነት እንዲደራጅም ምክረሐሳብ ቀርቧል።
ጥናቱ ሂደት ላይ እያለ መግለጫ መስጠት ያስፈለገውም የግፍ የዘር ጭፍጨፋ መፈፀሙን ማረጋገጥ በመቻሉ መሆኑን ቡድኑ በሰጠው መግለጫ አሳውቋል።
ጥናቱ የሚሸፍነው ጊዜ ትሕነግ ከደደቢት ተሻግሮ ወልቃይት ላይ ጦርነት ከከፈተበት ነሐሴ 28/1972 እስከ አካባቢውን ጥሎ እስከወጣበት 2013 ድረስ መሆኑን ቡድኑ አሳውቋል።
ጥናቱ ሲጠቃለል ምን ያህል ዜጎች በማንነታቸው ተለይተው እንደተጨፈጨፉና እንደተሳደዱ በቁጥር ይፋ ይደረጋል ተብሏል።
ስንታየሁ አባተ (ከጎንደር)
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!