በወሎ ግንባር ለተሰለፈው ጥምር ጦር ከ2 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ ተደረገ

ጳጉሜ 2/2014 (ዋልታ) የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር በወሎ ግንባር ለተሰለፈው ጥምር ጦር ከ2 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የእርድ ከብት እና በጎች ድጋፍ አደረገ፡፡

የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር የፓለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ታጠቅ ገድለአማኑኤል የኢትዮጵያን ህልውናና ክብር ለማሰጠበቅ በግምባር ለሀገር ህልውና እየተዋደቀ ለሚገኘው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ጥምር ጦሩ ደጀን መሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለጥምር ጦሩ በከተማዋ ከሚገኙ አምስት ክፍለ ከተሞች የተሰበሰበ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በሚገመት ወጪ 13 የእርድ ከብቶች፣ 200 ፍየሎች እና መሰል የምግብ ፍጆታ ድጋፎች ተደርገዋል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የሰሜን ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ጋሻው አስማማው  የወገን ጦር ለሀገር ሰላም በግንባር እየተፋለመ እንዳለ ሁሉ ደጀን ህዝብም አበረታች ስራዎችን እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ለጥምር ጦሩ የሚደረጉ መሰል ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተገልጿል፡፡

ለጥምር ጦሩ መንግስት እና ህዝብ በቅንጅት የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።

 

ሳራ ስዩም (ከግንባር)