በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ጋር ውይይት እየተካሔደ ነው

ነሐሴ 6/2013(ዋልታ) –በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ ከትግራይ ተወላጆች ጋር ውይይት እየተካሔደ ነው ።

በከተማዋ ከሚገኙ የትግራይ ተወለጆች የተወጣጡ የማህበረሰብ አካላት እና ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች በውይይቱ ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት ትግራይ ተወላጆች በሠጡት አስተያየት የትግራይ ህዝብ የፓለቲካ ፍላጎት እና የህዋት አላማ በጭራሽ የሚስማማ አይደለም ህዝቡ  ለውጥ ፈላጊ በመሆኑ ዲሞክራሲ እንዲያብብ አንድነት እዲጠናከር ለለውጡ ሲተጋ ይህንን የማይፈልገው የአሸባሪው ህዋህት ቡድን ለውጡን ለመቀልበስ እየሠራ ነው ብለዋል ።

ይህንን እኩይ  የአሸባሪውን ተግባር  መከላከል ለአንድ ወገን አልያም ለብልፅግና ፓርቲ የሚተው አይደለም ያሉት ተወያዬች የትግራይ ህዝብ ሀይሉን አሰባስቦ ከመላዉ ኢትዮጵያዊ ጎን ቆሞ አላማውን ሊያከሽፍ ይገባል ሲሉም አንስተዋል።

መንግስት የትግራይ  ህዝብ እንዳይጎዳ በትዕግስት እየወሠደ ያለውን እርምጃ ያደነቁት አስተያየት ሠጪዎቹ የትግራይ ህዝብን ከአሸባሪው የህዋሖት ቡድን ለይቶ ማየት ያስፈልጋል ብለዋል። ለዚህም ደግሞ መንግስት ቁጥጥሩን አጠናክሮ ለህዋት ተላላኪ ሆነው የሚሠሩ ወንጀለኞችን ሊለይ ይገባልም ሲሉ አክለዋል።

አሸባሪውን የህዋት ቡድን ዳግም እንዳያሰራራ መንግስት በቆራጥነት እና በቁርጠኝነት እርምጃ ሊወስድ ይገባልም ሲሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

እውነታውን ለዓለም በማሳወቅ ረገድ የዲፕሎማሲ ስራዎች በበቂ ሁኔታ እየተከናወነ ባለመሆኑ አሸባሪው የህዋት ቡድን በውሸት ምላሱ ዓለመን እያሳመነ በመሆኑ ሚዲያዎች፣ የመንግስት አካላት እና የፀጥታ አካላት አቅማቸውን አሙዋጠው ሊጠቀሙበት ይገባል ሲሉም የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

ይህም እውን እንዲሆን በአዲስ አበባ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በሚያስፈልገው ሁሉ ከመንግስት  ጎን እንደሚቆሙ ገልፀዋል።

(በድልአብ ለማ)