በወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ ከሀረሪ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ

ሐረር በአለም አቀፍ ደረጃ በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ ትምህርት እና ባህል ድርጅት (ዩኒስኮ) እ.ኤ.አ በ2003/4 በሰላም ፣ በትብብር እና የአብሮነት ከተማነት አለም አቀፍ ሽልማት እና እውቅናን አግኝታለች፡፡

ይህም የተለያዩ እምነት ያላቸው ህዝቦች ለዘመናት በሰላም፣ በአብሮነት፣ በመቻቻል በጋራ የኖሩባት እና ዛሬም የሚኖሩባት ከተማ በመሆኗ የተቀዳጀችው ክብር እና እውቅና ነው፡፡

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያጋጠመው ችግር በሰላማዊ መንገድ፤ በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት፤ በስክነትና  የቤተክርስቲያኗን ውስጣዊ አሰራር በተከተለ መንገድ እንደሚፈታ የክልሉ መንግስት ፅኑ እምነት አለው፡፡

ችግሩ ከተፈጠረበት ግዜ ጀምሮ በክልላችን በሐይማኖት ተቋማትና በህዝብ ደህንነት ላይ ችግር እንዳይፈጠር ፍጹም ፍትሃዊ እና ገለልተኛ በመሆነ መልኩ ስንሰራ ቆይተናል።

ሆኖም ግን በሀገራችን በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች መካከል የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ ፍጹም ምእመናዊ በሆነ መልኩ የሚንቀሳቀሱ ምእመናኖች እንዳሉ ሆኖ ስውር የፖለቲካ ዓላማቸውን በሃይማኖት ሽፋን ለማስፈጸም የሚሞክሩ ኃይሎች እንዳሉ ይስተዋላል።

በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረው ችግር ከሃይማኖት ጉዳይነት አልፎ እየተወሳሰበና በርካታ እኩይ ዓላማ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎችና የሽብር ሀይሎች ተቀናጅተው ሀገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ይህንን ተከትሎ በሁለቱም ወገን የካቲት 5 ቀን የተጠራው ሰልፍ ለክልሉ ሰላምና በህዝብ ደህንነት ላይ ችግር የሚፈጥር በመሆኑ በመንግስት ያልተፈቀደ እንደሆነ እየገለጸን መንግስት ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ህገመንግስታዊ ተግባርና ኃለፊነቱን ለመወጣት በሚያደርገው እንቅሳቃሴ ሁሉ መላው የክልሉ ሕዝብ አሰፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደረ‍ደርግ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

የሀረሪ ክልላዊ መንግስት

የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም

ሀረር