በወይብላ የተፈጠረውን ችግር ግብርኃይል ተቋቁሞ እየመረመረ እንደሚገኝ መንግሥት አስታወቀ

ጥር 19/2014 (ዋልታ) በጥምቀት በዓል ላይ በቡራዩ ከተማ አስተዳደር ወይብላ ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን የተፈጸመውን ድርጊት ግብርኃይል ተቋቁሞ እየመረመረ እንደሚገኝ መንግሥት አስታወቀ፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በወቅታዊ ጉዳይ በሰጡት መግለጫ ግብርኃይሉ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጣ እንደሆነ ገልጸው ውጤቱ ሲደርስ ለሕዝብ ይፋ ይሆናል ብለዋል፡፡

የጸጥታ ችግር በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ኃይማኖታዊ በዓሉ በሰላም መከበሩንም አስታውሰዋል፡፡

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደው ታላቁ ሩጫ በሰላም መጠናቀቁንም ገልጸዋል፡፡

በዓላቱ በሰላም ተከብረው መጠናቀቃቸው የአንዳንድ ሰላም ጠል ኃይሎች ሴራ መክሸፉን እንደሚያሳይም ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ አመላክተዋል፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባ የሚካሄደው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ እየተሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡