በዋጃና አካባቢው የሰፈነውን ሠላም ተከትሎ በአካባቢው በሸቀጦች ላይ የዋጋ ቅናሽ መታየቱ ተገለጸ

ታኅሣሥ 27/2015 (ዋልታ) በዋጃና አካባቢው የሰፈነውን ሠላም ተከትሎ በአካባቢው በሸቀጦችና ፍጆታ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ መታየቱን የዋጃ ሰኞ ገበያ ምርት አቅራቢዎች፣ ሻጮችና ሸማቾች ተናገሩ።

በቆቦ፣ በአላማጣ፣ ጥሙጋ፣ ዋጃና አካባቢው ሰላም መስፈኑን ተከትሎ የአካባቢው የገበያ ሥፍራዎች ወደቀደመ እንቅስቃሴያቸው ተመልሰዋል።

ገበያዎቹ ለነዋሪዎች አስፈላጊ የሆኑ የፍጆታ ምርቶችን በማቅረብ ጤናማ የግብይት ሥርዓት እያካሄዱ ሲሆን ሰኞ የሚውለው የዋጃና አካባቢው ገበያም ከፍተኛ ግብይት እየተካሄደበት ነው።

የዋጃ ሰኞ ገበያ ለምግብ ፍጆታነት የሚውሉ የግብርና እና ሰብል ምርቶች ከፍተኛ ግብይት የሚካሄድበት ትልቅ ሥፍራ ሲሆን ለመሸጥም ሆነ ለመሸመት ወደ ሥፍራው የሚያቀና ሰው ሁሉ እንደየአቅሙ ግብይት እያከናወነ ነው።

ከፍተኛ ግብይት የሚካሄድበት የዋጃ የሰኞ ገበያ ሥፍራ፤ ባለፉት ዓመታት በአካባቢው በነበረው ጦርነት ሻጭና ገዥ ተለያይተው መቆየታቸውን ገበያተኞቹ ያስታውሳሉ።

በወቅቱም ለከፍተኛ የኑሮ ውድነት በመጋለጥ በዕለት ተለት ኑሯቸው ላይ ጫና አሳድሮ መቆየቱን እንዲሁ።

ያም ሆኖ በቅርቡ በአካባቢው ሰላም መፈጠሩን ተከትሎም የግብይት ሥርዓቱ ወደነበረበት በመመለስ ሁሉም እንደየአቅሙ ጤናማ ግብይት እያካሄደ እንደሚገኝ ይናገራሉ።

በአካባቢው ሲካሄድ በነበረው ጦርነት ምክንያት የፍጆታን አቅርቦት ጨምሮ በሌሎች ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንደነበርና በገበያ ላይም ምርት ማግኘት አዳጋች እንደነበር አስታውሰዋል።