በዓለም ከተማ ዘመናዊ ቤተ መጽሐፍት ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

በዓለም ከተማ ዘመናዊ ቤተ መጽሐፍት

ታኅሣሥ 27/2014 (ዋልታ) ከ10 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በዓለም ከተማ የአርበኞች ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዘመናዊ ቤተ መጽሐፍት ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።

የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት የጤና ሚኒስትር ዴኤታና የአካባቢው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወካይ ዶ/ር አየለ ተሾመ እንደገለጹት ትምህርት ቤቱ ያለበትን ችግር ለመቅረፍ የአካባቢው ተወላጆችን በማስተባበር ነው ዘመናዊ ቤተ መጽሐፍት ለመገንባት ሥራ የተጀመረው።

ግንባታው ከ10 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከአንድ ሺሕ በላይ ተማሪዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚያስችል ዘመናዊ ቤተ መጽሐፍት ነው ያሉት ዶክተር አየለ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ እንሰራለን ብለዋል፡፡ ለግንባታውም በርካታ ግለሰቦች ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል።

የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና መምህራን በበኩላቸው ትውልድን ለመገንባት ትኩረት ሰጥተው የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና የአካባቢው ተወላጆች የጀመሩት ሥራ የተማሪዎችና የመምህራንን የረጅም ጊዜ ችግር የሚፈታና አርአያነት ያለው ተግባር ነው ማለታቸውን ኤፍቢሲ ዘግቧል።