በዓለም ዐቀፍ ውድድሮች ላሸነፉ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እውቅና ተሰጠ

ሚያዝያ 11/2014 (ዋልታ) በዓለም ዐቀፍ ውድድሮች ተወዳድረው በማሸነፍ እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ያገኙ 15 ወጣት ኢትዮጵያዊያን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያዎች እውቅና እና ሽልማት ተሰጣቸው።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኮሪያ ዓለም ዐቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ለቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያዎች እና ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ሽልማት ሰጥቷል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶቹ የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ ዕድገት ለማፋጠን አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኮሪያ ዓለም ዐቀፍ ትብብር ኤጄንሲ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ሚኒስትር ዴኤታው መንግሥት ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች የሚደገፉበትን ሥርዓት ለመዘርጋት እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ የኮሪያ ዓለም ዐቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ዳይሬክተር ሊ ቢዮንግ ኋ ኢትዮጵያ ለኢኖቬሽን ዘርፍ ሥራ ፈጠራ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት ኤጀንሲው እንደሚደግፍ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘኘው መረጃ አመላክቷል፡፡

ከአይ.ሲ.ቲ፣ ግብርና፣ ማምረቻ ዘርፍ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን እና ዲጂታል ዘርፎች የተውጣጡት 15 የቴክኖሎጂ አበልፃጊ ተሸላሚዎች በንግድ እና ቴክኒካል ጉዳይ ሥልጠና ሲሰጣቸው ቆይቷል።

በተሰጣቸው ስልጠና መሰረት ዓለም ዐቀፍ ውድድሮችን ተወዳድረው ከማሸነፍ ባሻገር በሀገር ውስጥም ከ200 በላይ የሥራ እድሎች፣ ከ100 ሺሕ እስከ 500 ሺሕ ብር ሀብት አግኝተዋል፡፡