“በዓሉን ስናከብር ከጥላቻ በመራቅ እርስ በእርስ  በመተሳሰብ  እንዲሆን እመኛለሁ” – ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አባባ፣ ሚያዝያ 15 ፣2014 (ዋልታ) – የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር በፍቅርና አብሮነት፤ አቅመ ደካማና ጧሪ የሌላቸውን ወገኖችን በመደገፍ እንዲሆን መልዕክት አስተላለፉ።

ለክርስትና እምነት ተከታዮች ለስቅለትና ትንሳኤ በዓል የእንኳን  አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ ፍቅር ለሰው ልጆች ሁሉ የሰላም ምንጭና መሰረት ነው ብለዋል፡፡  በዓሉን ስናከብር ከጥላቻ በመራቅ እርስ በእርስ በመተሳሰብ እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል።

“ለጠላቶቻችን እኩይ ሴራ ሳንበረከክና ሳንበገር የሀገራችንን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ከምንም ጊዜ በላይ አንድነታችንን አጠናክረን ማስቀጠል የሚገባን ጊዜ ላይ ነን” ሲሉ አንክለዋል።

ክርስቶስ ባስተማረን ፍቅር ራስን በማነጽ ከዘረኝነት፤ ጥላቻና ፅንፈኝነት በመላቀቅ እርስ በእርስ በመግባባት ላይ የተመሰረተ የውስጥ አብሮነትንና አንድነትን ማጎልበት ይገባናል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ከግላዊ ጥቅምና ፍላጎት በመላቀቅ፣ በመተጋገዝና በመተሳሰብ በታማኝነትና በቅንነት ህዝብን በማገልገል ለሀገር ያለንን ፍቅር በተግባር መግለጽም  ይገባናል ብለዋል ።

“ሁሉም ጠንክሮ በመስራትና ለሀገር እድገት የሚጠቅም ልማትን በማስቀጠል ጠንካራ የሆነች ሕብረ ብሔራዊት  ኢትዮጵያን ገንብቶ ወደ ብልፅግና ማማ ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ በእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸው።

ርዕሰ መስተዳደሩ ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር ለአቅመ ደከማ ወገኖች ማዕድ በማጋራትና ጧሪ የሌላቸውን አረጋዊያን በመደገፍ እንዲሆነም  መልዕክት አስተላልፈዋል ።