በ‘ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት’ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ይረጋግጣል- አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ

ኅዳር 25/2014 (ዋልታ) “በ’ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት’ የኢትዮጵያ አሸናፊነት ይረጋግጣል” ሲል አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ተናገረ።
ለኢትዮጵያ አሸናፊነት የአራቱም ማዕዘናት ልጆቿ ብርቱ የአንድነት ንቅናቄ ጉልህ ድርሻ እንዳለውም ተናግሯል።
አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በአፋር ክልል በመገኘት በአሸባሪው የሕወሓት ወራሪ ኃይል ከጭፍራ ከተማ ተፈናቅለው ለሰብዓዊ ቀውስ ለተጋለጡ ዜጎች የሚውል ድጋፍ አበርክቷል።
ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በሃምሳ ጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮችናንና በሽብር ቡድኑ ውድመት የደረሰበትን የጭፍራ ከተማ ጎብኝቷል።
በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጸው በጭፍራ ከተማ መገኘቱ ሁለት አይነት ተቃራኒ ስሜት ፈጥሮበታል።
ይኸውም የወገን ጦር በሽብር ቡድኑ ወራሪ ኃይል ላይ የተቀዳጀው አንጸባራቂ ድል እንዳኮራውና በተቃራኒው አሸባሪው ቡድን በወረራ በቆየባቸው ጊዜያት በዜጎች ህይወትና በንብረታቸው ላይ ያደረሰው ዝርፊያና ውድመት ደግሞ አሳዛኝና ልብ ሰባሪ እንደሆነ ገልጿል።
የሽብር ቡድኑ ወራሪ ኃይሎች ከተማዋን ለማውደም የፈፀሙት ጥፋት ሞራለቢስነት የተሞላበት እንደሆነም አንስቷል።
የክፋት ሁሉ ባለቤት የሆነውን የህወሃት የሽብር ቡድንን ጥፋት የሚሰማና የሚመለከት የትግራይ ሕዝብም በቃህ ሊለው እንደሚገባም አስገንዝቧል።
የሽብር ቡድኑን የጥፋት ጉዞ በመግታት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአፋር ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ህዝቡ እያደረጉት ያለው አኩሪ ተጋድሎ የሚደነቅ እንደሆነም ገልጿል።
በ’ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት’ ኢትዮጵያዊያን መስዋእትነቶችን ከፍለው ኢትዮጵያን አሸናፊ እንደሚያደርጓት ተናግሯል።
ወራሪው ቡድን በጭፍራና ካሳጊታ ከተሞች ቤተ እምነቶችን በማውደም ቅዱስ ቁርዓንን ጨምሮ ሌሎች ቅዱሳት መጻህፍትን ማቃጠሉ እንዳሳዘነውም ጠቅሷል።
በቀጣይም ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን በማካፈል፣ የወደሙ ቤተ እምነቶችንና መሰረተ ልማቶችን በመገንባትና ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች በመድረስ ጉዳት የደረሰበትን ሕዝብ መልሶ ማቋቋም ይገባል ሲልም ጥሪ አቅርቧል።
በግንባር ተሰልፈው ጠላትን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስቀጠል የህይወት መስዋእትነት እየከፈሉ የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የኢትዮጵያን ከፍታ እንደሚያረጋግጡ ጥርጥር የለኝም ብሏል።
ለሰራዊቱ ቤተሰቦች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ደግሞ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ የቤት ስራ ሊሆን እንደሚገባ መግለጹንም ኢዜአ ዘግቧል