በዚህ ዓመት 200 የአካቶ ትምህርት መስጫ ማዕከላት መቋቋማቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

መጋቢት 13/2013 (ዋልታ) – ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በዚህ ዓመት 200 የአካቶ ትምህርት መስጫ ማዕከላት መቋቋማቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ በልዩ ድጋፍ መስጫ ማዕከላት ዙሪያ ለርዕሰ መምህራንና ተዘዋዋሪ መምህራን ስልጠና ሰጥቷል።
በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎችን ተደራሽነት ለማረጋገጥ አዳዲስ ማዕከላት መቋቋማቸውንም አመላክቷል።
እያንዳንዱ ማዕከላት እስከ 35 የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ማስተናገድ የሚችሉ መሆናቸውም ተገልጿል።
ስልጠናው የተሰጣቸው ርዕሳነ መምህራንና ተዘዋዋሪ መምህራን ማዕከላቱን በአግባቡ በማደራጀት በተገቢው መንገድ መጠቀም እንዲችሉ ለማድረግ መሆኑንም በትምህርት ሚኒስቴር የልዩ ድጋፍና አካቶ ትምህርት ዳይሬክተር አቶ ተኽላይ ገብረሚካኤል ተናግረዋል፡፡
ይህም በሀገሪቱ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሁሉም ህጻናት የመማር መብታችው እንዲረጋገጥ የተያዘው ጥረት አካል መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።