በዛሬው ዕለት 74 ዕርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል መላካቸው ተገለጸ

ሚያዝያ 15/2014 (ዋልታ) በዛሬው ዕለት 74 ዕርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በአባአላ መንገድ በኩል ወደ ትግራይ ክልል መላካቸውን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደርሳቸው ለማድረግ የገባውን ቃል በማክበር ምቹ የሰብኣዊ ዕርዳታ ማጓጓዣ ሁኔታን ለመፍጠር እየሠራ መሆኑን አገልግሎቱ አስታውቋል።

ዛሬ ወደ ትግራይ ክልል ከተላኩት ተሽከርካሪዎች ውስጥ 6ቱ ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች ናቸው።

መንግሥት ከዓለም የምግብ ፕሮግራም እና ሌሎችም አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ነዋሪዎች ድጋፍ እንዲደርስ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በአስቸጋሪ ሁኔታ ወስጥ የሚገኙት የክልሉ ዜጎች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደርሳቸው ወራሪው ኃይል አሁንም ከያዛቸው የአፋር እና አማራ ክልል አካባቢዎች እንዲወጣ እና ምቹ የእርዳታ ማስተላለፊያ መስመርን መዘርጋት እንዲቻል እንዲሁም ከሚነዘቸው የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎች እንዲቆጠብ ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ጫና እንዲያደርግ መንግሥት ጥሪውን አቅርቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW