በዜጎች ላይ ጭካኔ በተሞላበት ጥቃት እየፈጸሙ ባሉ ወንጀለኞች ላይ መንግሥት ጠንካራ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
አቶ ደመቀ በሰብሳቢነት የሚመሩት ብሔራዊ የሰዎች መነገድ፣ ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ወደ ውጭ አገር መላክ ወንጀል መከላከል እና መቆጣጠር ብሔራዊ ምክር ቤት የ2013 ዓ.ም ዓመታዊ የውይይት መድረክ በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጸመ ያለውን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት አንሥተዋል።
በዜጎች ላይ የተፈጸመው ድርጊት ጭካኔ የተሞላበት የወንጀለኞች ተግባር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያውያን የሚጋሩት እና የወረሱት የዳበረ እሴት ባለቤቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አንዳንዶች በዜጎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት እየፈጸሙ ነው” ብለዋል።
“ይሄ ችግር ወደ የት እያመራ እንደሆነ ሁሉም ቆም ብሎ ሊያስብ ይገባል” የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።
ዜጎችን እየጨፈጨፉ ባሉ ወንጀለኞች ላይ መንግሥት ጠንካራ እርምጃ የሚወስድ መሆኑንም አቶ ደመቀ አረጋግጠዋል።
ለዚህም የተለያዩ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ መሆኑን አብራርተው፣ “ድርጊቱን ለማስቆም እና ወንጀለኞችን ለማደን የሁሉም ጥረት እና ትብብር ያስፈልጋል” በማለት ተናግረዋል።