በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖሩ አባወራዎች የመኖርያ ቤት የመገንባት ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ገለጸ

ግንቦት 17/2014 (ዋልታ) በቂርቆስ ክ/ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖሩ አባወራዎች የመኖርያ ቤት እንደ አዲስ የመገንባት ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ፡፡
ከ2014 በጀት አመት ባለፉት 9 ወራት ብቻ በተጎሳቆለ ቤት የሚኖሩ ዜጎችን አኗኗር ለመቀየር በሚያደርገው ጥረት 3ሺሕ ቤቶችን በማደስ ነዋሪዎችን ከመንገላታት መታደግ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል፡፡
በዚሁ ፕሮግራም አስተዳደሩ በ2013 መጨረሻ በቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 8 የልቤ ፋና ትምህርት ቤት አካባቢ 35 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃና ለሚኖሩ አባወራዎች መኖርያ ቤት እንደ አዲስ በአራት ዘመናዊ ብሎኮች የመገንባት ሥራ ማስጀመሩን አስታውሷል፡፡
ይህ ግንባታ ያለበትን ደረጃ በተመለከተም ከአራቱ ህንፃዎች ውስጥ አንዱ ሙሉ ለሙሉ ያለቀ ሲሆን ሁለተኛው የስኬለተን ሥራው መጠናቀቁን እንዲሁም ሦስተኛውና አራተኛው ቁፋሮና መሰረት ሥራ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ይህ ሥራ አስተዳደሩ ሲያከናውናቸው ከነበሩ ሌሎች ፈጣን ግንባታዎች አንፃር ወደ ኋላ የዘገየበት ምክንያት አንድ ግለሰብ ቦታውን አስመልክቶ ባቀረበው የፍርድ ቤት ክርክር እና እግድ ነው ተብሏል።
በዚህ ምክንያት ለ9 ወራት በክርክር ሂደት ሥራው እንዲጓተትና ነዋሪዎቹም አብላጫዎቹ በትምህርት ቤት ውስጥ እንዲቆዩ ሶስት አባወራዎች ደግሞ አስተዳደሩ ቤት ተከራይቶ እስካሁን አቆይቷቸዋል፡፡
ሆኖም ግን ሲጠናቀቅ 80 አባወራ እንዲይዝ ተደርጎ እየተሰራ ያለው ይህ ግንባታ ከ9 ወራት የፍርድ ቤት እግድ በኋላ በአሁን ሰአት ለግለሰቡ ተተኪ ቦታ ተሰጥቶት ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን ፕሮጀክቱ በፍጥነት እየተከናወነ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅና ለነዋሪዎች እንደሚተላለፍ የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል።
“ነገር ግን በአንዳንድ ሚድያዎች ከተከናወኑ መልካም ሥራዎች በላይ ይህ ከአቅማችን በላይ በሆነ ምክንያት የተፈጠረውን ችግር በማራገብ የተሳሳተ ገፅታ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ተገቢ አለመሆኑን አስተዳደሩ ያምናል ” ሲል የከተማ አስተዳደሩ ገልጿል፡፡
አስፈላጊ መረጃዎችን ከአስተዳደሩ ጋር ቀርቦ መጠየቅ እና ትክክለኛ መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ ማድረስ የሁሉም ሃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ተግባርም ሊሆን እንደሚገባ የከተማ አስተዳደሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡