የአሜሪካ ምርጫ ቀን እየቀረበ ነው። ከሰባት ቀናት በኋላ ማክሰኞ ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡ ወደ ዋይት ሐውስ ለመግባት የሚደረገውም ፉክክር በዚያው ልክ ተጋግሏል።
በሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ እና በዲሞክራቷ ካማላ ሃሪስ መካከል የሚደረገው የምርጫ ቅስቀሳ ከፖለቲከኞች በተጨማሪ በርካታ ታዋቂ ሰዎችን ያሳተፈ ሆኗል፡፡
ሙዚቀኞች፣ ተዋንያን እና በርካታ የጥበብ ሰዎች ለሚደግፉት ተወዳዳሪ ቅስቀሳን በማድረግ ፉክክሩን አጧጡፈውታል፡፡
በካማላ ሃሪስ በኩል ቢዮንሴ፣ ታይለር ስዊፍት፣ ኢሚነም፣ ሊዮናርዶ ዲካፕሪዮ፣ ማት ዴመን፣ ጄኒፈር ሎውረንስ እንዲሁም ሌሌች በርካታ የሆሊውድ ፈርጦች ለእጩዋ ድጋፋቸውን በተለያየ መንገድና በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው እየገለጹ ነው፡፡
የቀድሞዎቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እና ቢል ክሊንተንም ከነቤተሰቦቻቸው የካማላ ደጋፊዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡
እንዲሁም በሪፐብሊካኑ እጬ ዶናልድ ትራምፕ በኩል በርካታ ዝነኛ ሰዎች ድጋፋቸውን እየገለጹ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ፊፍቲ ሴንት፣ አምበር ሮዝ፣ ብሪትኒ ስፒርስ፣ ዳና ዋይት እና ሌሎች በርካታ ዝነኞች ይገኛሉ፡፡
ቴስላ የተባለው የመኪና አምራች ኩባንያ እና የኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ባለቤት የሆነው ኤሎን መስክ በዘንድሮው ምርጫ ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ እንዲያሸንፉ በሰፊው እየቀሰቀሰ ይገኛል። ከዛም አልፎ ትራምፕን ለሚደግፉ መራጮች በሎተሪ እጣ መልክ በየሳምንቱ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እየሰጠ ነው፡፡
እንደዚህ በበርካታ ዝነኞች እና ታዋቂዎች ድጋፍ እያገኘ ያለው የሁለቱ እጬ ተወዳዳሪዎች ቅስቀሳ ምርጫውን በተጽእኖ ስር እንዲወድቅ ደርገዋል የሚሉ ዜጎች አሉ፡፡
መራጮች በትክክል የሚጠቅማቸውን አስበው ከመምረጥ ይልቅ በሚወዷቸው ዝነኞች ለሚደገፉት ተወዳዳሪዎች ድምጻቸውን ሊሰጡ ይችላሉ የሚል አስተያየት እየተሰጠ ነው፡፡
በአንጻሩ ሌሌች ደግሞ “ዝነኞችም የፈለጉትን ፖለቲካ ማራመድ እና መደገፍ ይችላሉ፤ ሌሎች መራጮች ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ የለም” በማለት ይከራከራሉ፡፡
እርስዎ ምን ያስባሉ? በዝነኞች የታጀበው የአሜሪካ ምርጫ ቅስቀሳ ድምጽ አሰጣጡ ላይ ተጽእኖ ይኖረው ይሆን? ሀሳባችሁን በአስተያየት መስጫው ላይ ያጋሩን፡፡