በደም መፍሰስ የበርካታ እናቶች ህይወት እየተቀጠፈ መሆኑ ተነገረ

ጥር 21/2014 (ዋልታ) የጤናማ እናትነት ወር “በማንኛውም ሁኔታ ከወሊድ በኋላ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት እጅ ለእጅ ተያይዘን እንግታ” በሚል መሪ ቃል በደሴ ከተማ እየተከበረ ነው።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንደገለጹት ከወሊድ ጋር በተያያዘ አሁንም ለሞት የሚዳረጉ እናቶች ቁጥር ከፍተኛ ነው።
በኢትዮጵያ በየቀኑ ከ30 በላይ በዓመት ደግሞ 11 ሺሕ የሚሆኑ እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ህይወታቸው እያለፈ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
በቀላሉ መከላከል የሚቻለው ጉዳይ ተባብሮ ባለመስራትና በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ከወሊድ በኋላ በሚፈስ ደም የበርካታ እናቶች ህይወት እየተቀጠፈ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሸባሪው ሕወሓት የወደሙ ጤና ተቋማትን መልሶ በማቋቋም ነፍሰጡር እናቶች በጤና ባለሙያ ታግዘው እንዲወልዱ ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተመላክቷል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ጋሹ ክንዱ በበኩላቸው በደም መፍሰስ የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።